የሚክያስን ‹ወልድ ሥጋን ነስቷል!›ን እንቀበል?

የሚክያስን ‹ወልድ ሥጋን ነስቷል!›ን እንቀበል?
በተካልኝ ዱጉማ
በስነ-መለኮት ጥናት እና ክርክር ውስጥ የቃላት ትርጓሜ እና አጠቃቀም ዋነኛ ስፍራ አላቸው፡፡ ቃላት በተለያዩ አውድ ውስጥ የተለያየ ትርጉም ሊኖራቸው ይችላልና፡፡ በዚህ ትንሽ መጣጥፍ ውስጥ ለወንድማችን ሚክያስ በማቴቴስ መጽሔት ቁጥር 8 ሐምሌ 2000ዓም ላይ ‹‹ወልድ ሥጋን ነስቷል!›› በምል ርዕስ በወጣው መጣጥፍ ውስጥ ወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት ተዋችሁት የተባልነው ‹‹መጸሐፍ ቅዱሳዊ እውነት›› ‹‹ቃለ ወልድ ከእናቱ ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን፣ ከነፍሷ ነፍስን ነስቷል፡፡›› ብዥታን በሰው አእምሮ ውስጥ ስለምፈጥር ምን ያህል መጸሐፍ ቅዱሳዊ እውነት እንዳለው እንደሁም በጥንቃቄ ካልታሰበበት ወዴት ሊያመራ እንደሚችል አሳያለሁ፡፡ በማጠቃለያም ስነ-መለኮታዊ ሀሳቦችን እና ቃላት ስንወስድ የሀሳቡ በለቤቶችን እንዴት እንደተጠቀሙበት ማስተዋሉ አስፈለጊ እንደሆነ ምክሬን በመለገስ አጠናቅቃለሁ፡፡
ወንድማች በድፍረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን መለያ መፈክር የሆነውን ‹‹እግዚአብሔር ወልድ ከሰማያት ሰማይ ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋዋን፣ ከነፍስዋም ነፍስ ነሥቶ›› የሚል እንድምታ ያለውን ሀሳብ በመጣጥፉ ላይ አቅርቦአል፡፡ ልንጠይቀው የሚገባን ጥያቄ ይህ ምን ማለት ነው? መጸሐፍ ቅዱሳዊ መሰረቱ እስከ ምን ድረስ ነው? የሚል ነው፡፡
የአምላክ ሰው የመሆን ምሥጢር በቤተክርስትያን ታሪክ ውስጥ ብዙ የቤተክርስትያን አባቶችን እንዲያስቡበት እናም ምን ማለት እንደሆነ ለማስረዳት እንዲሞክሩ አስገድዶአቸዋአል፡፡ ዛሬ የቤተክርስትያን አባቶች ስለ ክርስቶስ ሰውነት ምን አሉ የሚለውን ለመዳስስ ሳሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን ከማርያም ነሥቶአል ማለት ምን ማለት እንደሆነ አሳያለሁ፡፡
ነሣ የሚለው ቃል አምስት ትርጓሜዎች አሉት ‹‹ከለከለ፣ወሰደ፣አራቀ›፤ ‹ተቀበለ፣ወሰደ›፤ ‹ያዘ፣ ጨበጠ›፤ ‹ቀነሠ፣አጎደለ፡፡ (ሥጋ ነሣ)፤ተፀነሰ፣ ሰው ኸነ፣ ሥጋ ለበሰ፡፡› እና ‹ቻለ፣ ወሰነ› ›› ከነዚህ የቃሉ ፍችዎች ከዚህ መጣጠፍ ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ያለው ተፀነሰ፣ ሰው ኸነ፣ ሥጋ ለበሰ ሚለው ነው፡፡ ወንድማችን በጽሑፉ ውስጥ ማለት የፈለገው የክርስቶስ ፅንሰት የማርያምን የሴት ፍሬ ተጠቅሞ እንደሆነ ለማሳየት ከሆነ ሊሆን ስለሚችል ምንም ጥያቄ አይኖረኝም፡፡ ስለሚችል ያልኩበት ምክንያት መጸሐፍ ቅዱስ ክርስቶስን የተጸነሰበትን ሕዋሳዊ ቀመር ስለማይገልጽ በድፍረት ይህ ብቻ ነው ማለት ማንም ስለማይችል ይህ አንዱ ሊሆን የሚችል መላ ምት ሊሆን ስለሚችል ነው፡፡
ነግር ግን የወንድማችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን በዚህ ረገድ ያላትን ‹‹ትክክለኛ›› አመለካከት (ትክክለኝነቱ ለእርሱ) በመደገፍ ‹‹ቃለ ወልድ ከእናቱ ሥጋን አልነሣም ወይም አልተካፈለም ማለት ከኑፋቄ የሚያስመድብ የተሳሳተ ትምህርት ነው፡፡ የቅድስት ማርያምን ‹‹አማላጅነት›› መሞገት ቢያስፈልግ እንኳ ይህንን ድነት ያገኘንበት መሠረታዊ እውነት ጨፍልቀን መሆን የለበትም›› ብሎናል፡፡ ስለዚህ የእርሱ ሥጋ መንሣት እሳቤ የተመሠረተው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የቤተክርስትያን ምሥጢረ ሥጋዊ አስተምህሮ ላይ ስለሆነ ይህንን በጥንቃቄ መመርመሩ አስፈላጊ ይሆናል፡፡
የኢትዬጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ምሥጢረ ሥጋዌም እንዲህ ነው
‹‹ ምስጢረ ሥጋዌ ከሦስቱ አካላት አንዱ፡- እግዚአብሔር ወልድ ከሰማያት ወርዶ ከቅድስት ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን፣ ከነፍስ ነፍስ ነሥቶ በሥጋ የመገለጹ፣ አምለክ ሰው፣ የመሆኑ ምሥጢር ነው፡፤ ‹‹ቃል ሥጋ ሆነ በእኛም አደረ›› (ዮሐ 1፡14)፡፡….መለኮት ከሥጋ ሥጋ ከመለኮት ጋር ያለመለወጥ፣ ያለመቀላቀል፣ ያለ መለያየትና ያለ መከፋፈል በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነ፡፡ ሰው ከመሆኑ አስቀድሞ ሰውም ከሆነ በኋላ አንድ ወልድ አንድ ክርስቶስ ነው፡፡››
ይህ እንግዲህ የቤተክርስትያኒቷ ኦፊሴላዊ የእምነት መግለጫ ነው፡፡ ‹‹ምሥጢረ ሥጋዌ ማለት ዘላዓለማዊው እግዚአብሔር ወልድ ሰው የሆነበት ማለት የሰውን ሥጋ የለበሰበት ምሥጢር ማለት ነው፡፡… ወልድ እግዚአብሔር ቤዛ በመሆን የሰውን ልጅ ከሞት ለማዳን መለኮቱን ሕማምን እና ሞትን ሊቀበል ከሚችል ከሰውነት ጋር ያዋሐደበት ነው›› በአንድ ወቅት የኢቨንጀልካል ቲዬሎጅካል ኮሌጅ ፕርንስፓል እና አስተማሪ የነበሩት ዶ/ር ስቲቨ ስትራዊስ ስለ ኢትዬጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ምሥጢረ ሥጋዌም ሲገልጹ ‹‹የኢትዬጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያ በትስብዕት ወቅት (ቅጽበት) በመንፈስ ቅዱስ ሥራ አማካኝነት ዘላላማዊው የእግዚአብሔር ልጅ ከድንግል ማርያም በተወሰደ ሥጋ እና ነፍስ ሰዋዊነትን ከራሱ ጋር አዋሀደ፡፡›› ብለዋል፡፡ ይህም ምን ማለት እንደሆነ ስያብራሩ እንዲህ ነው ያሉት ‹‹በጽነስት ግዜ እነዚህ ሁለት ባህሪያት፤ መለኮታዊው የእግዚአብሔር ልጅ ባህሪይ እና ከማርያም በተወሰደው ፍጹም የሆነው ሰዋዊ ባህሪይ ወደ አንድ አካል እና ወደ አንድ ባህርይ ተዋሃዱ፡፡›› ስለዚህ ከማርያም ተወሰደው (የተነሣው) ሥጋ እና ነፍስ ፍጹም ከሆነ ወደቴ እያመራን እንደሆነ ተመልከቱ፡፡ የማርያምስ ሥጋ እና ነፍስ እንዴት ፍጹም ሊሆን ቻለ ወደሚል ጥያቄ ስለሚያመራን ማለቅያ ወደ ሌለው ነገር ማምራታችን ነው:: ፈረንጆቹ Infinite regress ወደ ሚሉት፡፡
ዓሥራት ገብረማርያምም የተባሉት የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን የመጸሐፍ ቅዱስ ምሁር ስለ ውሕደቱን ሲገልጹ ‹‹ሥጋን በተዋሐደ ጊዜ ነፍስ ያለውን ሥጋ ነው እንጅ ነፍስ የሌለውን ሥጋ አልተዋሐደም፡፡›› ብሎታል፡፡ ይህ ሁላችንም የምንቀበለውን የክርስቶስን ሰው መሆንን ስለሚያመለከት ምንም ጥያቄ አይኖረውም፡፡ ነገር ግን ጥያቄው ያለው ውሕደቱ ከማርያም ሥጋ (ዘር) እና ነፍስ ጋር ከሆነ የክርስቶስ ከኃጢአት ውጭ መሆኑ ከማርያም ንጽህና ወይስ ከመለኮት ባህር የተነሳ ይሆን? የሚለው ሲሆን የቤተክርስትያንቷ ኦፊሴላዊ የእምነት መግለጫ ግን እንዲህ ነው የሚለውነ
‹‹አምላክን በድንግል ፀንሳ በድንግልና የወለደችው እመቤታችን ድንግል ማርያም ከአዳም ዘር የተላለፈ ኀጢአት(ጥንተ አብሶ) ያላገኛት መርገመ ሥጋ ለፍስ የሌለባት ገና ከመወለዷ አስቀድሞ በአምላክ ኀሊና ታስባ ትኖር ነበረች በሰው ልማድና ጠባይ ከሚደርሰው ሥጋዊ አሳብና ፍቃድ ሁሉ የተጠበቀች ከተለዩ የተለየች ንጽሕት ቅድስት ቅዱሳን ናት፡፡ …. እመቤታችን በውስት በአፍኦ በነፍስ በሥጋ ቅድስት ስለሆነች እግዚአብሔር ለልጁ ማደርያ መርጦታል፣ ማኀደረ መለኮት እድትሆን አድርጓታል፡፡ አምላክን ለመውለድ ያስመረጣትና ያበቃት ድንግልናዋ ንጽሕናዋ ነው፤፤… ንጹሕ ነፍስ ንጹሕ ልቦና ለእመቤታችን ገንዘቦቿ ናቸው፡፡››

ቤተክርስቲያኗ የክርስቶስ ከኃጢአት ነጻ የመሆኑ የአስተምህሮ ምሥጢር ያለው የማርያም ንጽህና ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም የቤተክርስትያኗ የእምነት መግለጫ ‹‹በአፍኦ በነፍስ በሥጋ ቅድስት ስለሆነች እግዚአብሔር ለልጁ ማደርያ መርጦታል›› ይላልና፡፡ የክርስቶስን ከማርያም ሥጋን እና ነፍስን አጥብቀው የሚያስተምሩት ሰው በመሆን ከእኛ እንደ እንዱ እንደሆነ ለማሳየት ሳይሆን የማርያምን ንጽሕና ትምህርት ለማስተማር እንደ መሳርያ ስለሚያገለግላቸው ነው፡፡ ይህ የሚያሳየን ወንድማችን እንድንቀበለው ካልሆነ ግን ኑፋቄአዊያን እንደምንሆን ያስገደድ ‹እውነት› ነው፡፡ ታዲያ የክርስቶስ ከኀጢአት ንጹሕ የመሆኑ እውነት ምክንያት ከማርያም ንጽሕና እንደሆነ የሚያስተምረውንት ትምህርት እንቀበለው ይሆን? ምንስ ምርጫ ይኖረናል? ካልተቀበልን ኑፋቄ መባላችን አይደል?
እርግጥ ነው በኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አማኞች ዘንድ ትክክል ያልሆነ መረዳት ሊኖር ይችል ይሆናል ነገር ግን ይህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን እምነት መሰረት የሆነውን ንጽሕት፣ ከአዳም ዘር የተላለፈ ኀጢአት (ጥንተ አብሶ) የሌለባትን የማርያምን ሥጋ (ዘር) እና ነፍስ ክርስቶስ ወስዶአል ወደ ሚል ድምዳሜ በግዴታ እንድንሄድ ግን አያስገድደንም፡፡ የክርስቶስ ፍጹም ከኀጢአት ንጹሕ መሆን ግን የወንጌላዊያን አማኞች መሰረታዊ እምነት ነው፡፡
ከወንድሜ መጣጥፍ የምነቅፈው ክርስቶስ ከማርያም ሥጋ መንሣቱን ሣይሆን ሥጋ ነሣ የሚለው አመለካከት ከኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ስነ-መለኮታዊ አስተምህሮ አፈር ላይ የበቀለ መሆኑን ነው፡፡ ማስረገጫ ይሆነኝ ዘንድ ወንድሜ ያለውን ልጥቀስ ‹‹…ዓይኖቻችንን ከፍተን እዚያ ሠፈር ያለውን መልካሙን ዘር ለመቃረም እንሞከር›› ወንድማችን እነርሱ በዚህ ረገድ ልክ ናቸውና እንቀበላቸው ነው እያለን ያለው፡፡ እኔ ግን በኦርቶዶክሳዊያን እሳቤ መሰረት ሥጋን ነሣ የሚለው ቃል ስነ-መለኮታዊ ችግር እንደለበት በማሳየት እነርሱ ልክ አይደሉም ባይ ነኝ፡፡ እነርሱ የሚሉት ከአዳም ዘር የተላለፈ ኀጢአት (ጥንተ አብሶ) ከሌለባት ከማርያም ሥጋ እና ነፍስን ነስቷል ስሆን እኛ ወንጌላዊያ አማኞች የሚናምነው ሥጋን ከማርያም መንሣቱን ነገር ግን የክርስቶስ ከኀጢአት ውጭ የመሆኑ ምስጥር ያለው በእርሱ አምላከነት እና በመንፈስ ቅዱስ ሥራ እንጅ በነሣው ሥጋ እና ነፍስ ንጽሕና ላይ አለመሆኑን ነው፡፡ ምክንያቱም በኦርቶዶክሳዊያን አስተምህሮ መሰረት ክርስቶስ ሥጋ ነሣ የተባለበት ማርያም የአዳም ዘር የሆነችና እንደማንኛውም ሰው የውርስ ኃጢአት ያለባት በመሆኑ ነው፡፡ እርሷም ከኀጢአት የነጻች ነች ቢሉም እንዴት እንደሆነ ግን በቅ መልስ ስሰጡ እስከ ዛሬ አልተመለከትኩም፡፡

የሰው ልጆች ሁሉ የውርስ ኃጢአት (ጥንተ አብሶ) እንዳለባቸው፤ ማርያምን ከዚህ ነገር ተካፋይ እንደሆነች ብዙ መጸሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ መረጃዎች አሉ፡፡ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል ዘፍጥረት 3' 6:5' ኢዮብ 15:14'መዝሙር 51:5' ኤርምያስ 17:9-10፣ ማርቆስ 7:21-23፣ ሮሜ 1:18-25፣ 5፡12-19፡፡ እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት የመጸሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የሚያስረግጡልን ከሰው ልጆች መካከል ከዚህ የኀጢአት አብሶ ነጻ የሆነ ሰው አለመኖሩን ነው፡፡ ይህ ታድያ የወንድማችንን ክርስቶስ የማርያምን ንጹህ የሆነ ሥጋ ክርስቶስ የመንሣቱን ‹‹ኦርቶዶክሳዊ›› የአስተምህሮአዊ ግብዥያ ውድቅያ አያደርገውም ትላላችሁ? ወደ እዛኛውስ መንደር ይህንን አስተምህሮ ፊለጋ መሄድ ያስፈልጋል? በጭራሽ! ነገር ግን እዚሁ በመንደራችንን ያለውን ነገር ግን ያላስተማርነውን እውነት እናስተምር፡፡
ስነ-መለኮታዊ ቃላት እና ሀሳብን ስንጠቀም የሀሳብ ባለቤቶች ያንን ቃል ወይም ሀሳብ በምን ቅድመ እሳቤ እንደተጠቀሙበት መመልከቱ ከብዙ ስህተት ሊታደገን ስለሚችል ከመጻፋችን ወይም ከማስተማራችን በፊት የሰዎችን ስነ-መለኮታዊ እሳቤ ምን እንደሆነ በጥንቃቄ ብንመረምር ጥሩ ነው ስል ምክሬን በመለገስ አጠናቅቃለሁ፡፡

ሚክያስ በላይ ክርስቶስ ወልድ ሥጋን ነስቷል! ማቴቴስ መጽሔት ቁጥር 8 ሐምሌ 200ዓም ገጽ 27
ዝኒ ከማሁ ገጽ 27
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን እምንት፣ ሥረዓተ አምልኮና የውጭ ግንኙነት (ትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት፣ አዲስ አበባ፣ 1996) ገጽ 25
ቤተክርስትያንን ታረክ ለሚያጠና ሰው በክርስቶስ ማንነት ላይ ለተነሱ ትያቄዎች እና የስህተት ትምህሮቶች የጥንቷ ቤተክርስትያን እንዴት መልስ ትሰጥ እንደነበረ መመልከት ይቻለል፡፡
ደስታ ተክለ ወልድ፣ ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃለት (አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፣አዲስ አበባ፣ 1970) ገጾች 1981-2
ዝኒ ከማሁ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን እምንት፣ ሥረዓተ አምልኮና የውጭ ግንኙነት (ትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት፣ አዲስ አበባ፣ 1996) ገጽ 25-27
ዓሥራ ገብረማርያም፣ ትምህርተ መለኮት 3ተኛ ዕትም ገጽ 115፣ 125
ስትቨ ስትራዊስ Jesus in the Oriental Orthodox church: A Case study from Ethiopia, 2003
ስትቨ ስትራዊስ እኝህ ሰው ስለ ኦርቶዶከስ ቤተክርስትያን በኦርቶዶክሳዊን የተጻፉ ማስረጃዎችን በጽሑፋቸው ስላካተቱ ማነጻጸር ይቻላል፡፡
ዝኒ ከማሁ ገጽ120
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን እምንት፣ ሥረዓተ አምልኮና የውጭ ግንኙነት (ትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት፣ አዲስ አበባ፣ 1996) ገጽ 49 የስር መስመር እና እንድታይ ያደመቅሁት እኔ ነኝ፡፡
ዝኒ ከማሁ ገጽ 49 የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን የሚሥጢረ ሥጋዎ አስተምህሮት መሰረታዊ አላማው የክርስቶስን ከእኛ አንዱ እንደሆነ ማሳየት ሳይሆን የማርያምን ወላድተ አምላክንትን ለማሳመን የተቀነባበረ ትምህርት ነው፡፡ ስለዚህ የዚህን ትምህርት መሰረተ እሳቤ ሳንረዳ እንዳለ መቀበሉ በኃላ ልንወጣው የማንችለው ችግረ ውስጥ ስለሚከተን እኔ የማምነበት እንድሁም መጸሐፍ ቅዱስ በእርግጥ የሚያስተምረውን የክርስቶስን ሙሉ ሰውነት ማስተማሩ አስፈለግ ነው፡፡ ነገር ግን መጸሐፍ ቅዱስ ከምለው በላይ መሄዱ አስፈላግ አይደለም ምክንያቱም ይህ ማላ ምት እንጅ ተጨባጭ የሆነ መጸሐፍ ቅዱሳዊ መረጃ ስለማይኖረው ነው፡፡ ክርስቶስ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ እንደ ነበር እና እንደሆነ እንድሁም ከእኛ እንደ እንዱ እንደሆነ ብዙ መጸሐፍ ቅዱሳዊ መረጃዎች አሉን፡፡ ነገር ግን እንዴት ይህንን ሰዋዊውን ተፈጥሮ እንደተጎናጸፈ ግን ከመወለዱ እና እንደ ሰው ሆኖ ከመኖሩ በለይ የሚናውቀው ነገር የለም፡፡
ሚክያስ በላይ ክርስቶስ ወልድ ሥጋን ነስቷል! ማቴቴስ መጽሔት ቁጥር 8 ሐምሌ 200ዓም ገጽ 20፣27

ሚላሪድ ጄ. ኤርክሰን፣ Christian Theology, (Grand Rapid, michigan,1985) p.756 ምንም እንኳ ኤርክሰን በዚህ ክፍል የሚያወሳው የድንግል መውለድ አስተምህሮ ከክርስቶስ ከኀጢአት የለሽ ፍጽምና ጋር እንደማይገናኝ ብሆንም ነግር ግን የማርያሚን ጥንተ አብሶ ተካፋይንት ስለሚገልጽ ልወስደው ተገደድኩኝ፡፡

Comments